ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከስዊድን አቻቸው ጋር በኒዮርክ ተገናኙ፤

ጥር 02፣2009 ዓ.ም.

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከስዊድን አቻቸው ማዳም ማርጎት ዎልስቶርም ጋር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የግጭት መካለከል እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ከተያዘው ስብሰባ ጎን ለጎን ጥር 02፣2009 ዓ.ም ተገናኝተዋል::

ሁለቱም ሀገሮች የፀጥታው ም/ቤት አዲስ ተለዋጭ አባላት ሆነው  ስራቸውን እንደመጀመራቸው ሚንስትሮቹ  የጋራ የሆኑ ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች  በትብብር መስራት በሚችሉበት  ዙሪያ ተወያይተዋል::

ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት  የግጭት መካለከል እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ስብሰባ በአለም በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አከባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች ምላሽ ለመስጠት እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል::

ዶ/ር ወርቅነህ ፎረሙ አወንታዊ እንዲሆን ሀገራቸው የተቻላትን ሁሉ ለማድርግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል::

በሌላ በኩል ዶ/ር ወርቅነህ የስዊድን ጠ/ሚንስትር ስቴፋን ሎፍቬን እ.ኤ.አ 2015/16 ኢትዮጵያን ሶስት ጊዜ መጎብኝታቸውን አስታውሰው፣ ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማሻሻል እንደረዳው ተናግረዋል::

ስዊዲን  የፀጥታው የምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር ስፍራን እንደመሆኗ በተለያዩ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የም/ቤቱ አባላት ጋር በቅርበት መስራት እንደምትፈልግ ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማርጎት ዎልስቶርም ተናግረዋል። ሚኒስትሯ አያይዘው የፀጥታው የምክር ቤት አባላት ለሚቀጥሉት ጊዜያት በትብብር መንፈስ እንደሚሰሩ ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል::