ኢትዮጵያና ጃፓን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ከፍ ለማድረግ ተስማሙ፤

 ጥር 2፣2009 ዓ.ም.

በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ግጭትን መከላከልና ዘላቂ ሰላምን ማስቀጠል በሚል በሚደረገው ፎረም ለመሳተፍ ወደ ኒዮርክ ያቀኑት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከፎረሙ አስቀድሞ በትናንት ነው ዕለት(ጥር 1፤2009 ዓ.ም.) ከጃፓኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤት ሚስተር ኖቡኡ ኪሽ ጋር የተወያዩ ሲሆን ሁለቱም አካላት በመካከላቸው ያለውን ትብብርን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጃፓን የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ እንደ እንደሆነች እና ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር የጋራ በሆኑ በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርበት መስራት እንደምትፈልግ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል። ክቡር ሚኒስትሩ ጨምረው ኢትዮጵያና ጃፓን እጅግ በጣም ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው ብለዋል። የካይዘን ፍልስፍና ለኢትዮጵያ የተደረገ የጃፓን ስጦታ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጰያና ጃፓን ሌሎች አዳዲስ የትብብር ዘርፎችን ለማስፋት ይሰራሉ ብለዋል ሚኒስትር ወርቅነህ።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ጃፓን የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እንደመሆናቸው መጠን ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በከጃፓን ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል። ዶ/ር ወርቅነህ ኢትዮጵያ ሰላም በሌለው ቀጠና ውስጥ የሰላም ደሴት መሆኗን ተናግረው፣ ሁለቱ አገራት በደቡብ ሱዳን እና በሌሎች አገሮች ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት በቅርርብ ሊሰሩ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤት ሚስተር ኖቡኡ ኪሽ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗን በማስመልከት እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። ኢትዮጵያ ለአለፉት ከአስር ዓመታት በላይ ያስመዘገበችውን የባለ-ሁለት አሀዝ የምጣኔ ኃብት እድገት በማስታወስ፣ የጃፓን መንግስት የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደረጉ እና ቢዝነስ እንዲሰሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።  የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት(JETRO) በአዲስ አበባ ጽ/ቤት ማቋቋሙ ለጃፓን ኩባንያዎች ትልቅ እድል ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።  ሚኒስትር ዴኤታው በናይሮቢ ኬንያ እ.ኤ.አ. ኦገስት 2016 በስኬት የተጠናቀቀውን 6ኛውን የቶክዮ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ (TICAD VI) አውስተው፣ አፍሪካን በአጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን አመስግነዋል።